october, 2017 - embassy of ethiopia,...

15
October, 2017 የኢትዮዽያ ኤምባሲ ስቶክሆልም ሀገሬ ወርሀዊ ቡለቲን

Upload: others

Post on 23-Oct-2020

1 views

Category:

Documents


0 download

TRANSCRIPT

  • October, 2017

    የኢትዮዽያ ኤምባሲ

    ስቶክሆልም

    ሀገሬ ወርሀዊ ቡለቲን

  • 2

    ማ ው ጫ ገ ጽ

    10

    1. የፖለቲካ አምድ ……………………

    1.1 አገራችን በተ.መ.ድ የፀጥታው ምክር

    ቤት

    2. የኢኮኖሚው አምድ ………………………

    • የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማትና ኢኮኖሚያዊ

    ፋይዳው

    • ግንቦት 20 - የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መሰረት

    እንቅስቃሴና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ …………

    3. የዳያስፖራ አምድ ……………………

    • የኤምባሲው ያለፉት አራት ዓመታት

    አፈጻጸም ዳሰሳ

    ይህን ያውቁ ኖሯል

    7

    8

    1.2 የ2017/18 ህዳሴ ጉዞ ፍኖተ ካርታ

    1

    4

    13

    7

  • 1

    አገራችን ኢትዮጵያ ለፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ

    አባልነት በከፍተኛ ድምጽ ከተመረጠችበት እ.ኤ.አ ጁን

    28 ቀን 2016 ወዲህ ባሉት ጊዜያት ዘርፈ ብዙ

    ኃላፊነቶችን ተወጥታለች። የፀጥታው ም/ቤት ተለዋጭ

    አባል ሆና በምታገለግልባቸው ሁለት ዓመታት ቅድሚያ

    ትኩረት የምትሰጥባቸውን ጉዳዮች ለይታ ወደ ተግባራዊ

    እንቅስቃሴ መግባቷ ይታወቃል። በዋነኛነትም

    በአካባቢችን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን፣

    ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ባቀደችው

    መሰረት በዚሁ ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ

    ትገኛለች።

    አገራችን የፀጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባል ሆና

    ከተመረጠችበት ጊዜ ጀምሮ የአህጉራችን አፍሪካ

    ተወካይ እንደመሆኗ ለአህጉሪቷ ችግሮች ዓለም አቀፉ

    ማህበረሰብ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ በማድረግ

    ረገድ ባደረገችው እንቅስቃሴ ላይ በማተኮር ባለፈው

    አንድ ዓመት ያከናወነቻቸውን ተግባራት ማየት ተገቢ

    ይሆናል።

    አገራችን ለአፍሪካ ሀገራት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ

    እንዲያገኙ አዎንታዊ ተፅዕኖ የማሳደር ትርጉም ያለው

    ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች። የፀጥታው ምክር ቤትን

    ለአንድ ወር በፕሬዚዳንትነት የመምራት ስልጣን

    ተጠቅማ በዚህ አጭር የሃላፊነቷ ጊዜ አዎንታዊ ተጽዕኖ

    የማሳደር ዕድሏን በአግባቡ ተጠቅማለች።

    ለዚህም ዋነኛ ማሳያ የሚሆነው ከአንድ ዓመት በፊት

    የፀጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ስትመረጥ ቃል

    በገባችው መሰረት፣ ለዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር

    ተልዕኮ የሚሰማሩ የመንግስታቱ ድርጅት ወታደሮች

    ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ የማሻሻያ ሰነድ አዘጋጅታ

    ከማቅረቧ ባሻገር ሰነዱ 15 አባላትን ባቀፈው የፀጥታው

    ም/ቤት በሙሉ ድምፅ መፅደቁ ነው። የተ.መ.ድ መደበኛ

    ጉባኤ ላይ ከተመከረባቸው ዓለም አቀፍ ጉዳዮች

    መካከል በሰላም ማስከበር ተግባር ላይ የተሰማሩ

    ወታደሮች በሴቶች ላይ የሚያደርሱት የአስገድዶ

    መድፈር ወንጀል በተመለከተ በህግ ፊት ቀርበው

    እንዲጠየቁ ስለማድረግ ይገኝበታል። በጉባኤው ላይ

    የአገራችን የተ.መ.ድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች

    ህዝባዊነትና አርዓያነት አድናቆት የተቸረው ሲሆን፣

    አገራችን በምግባረ ብልሹ የተ.መ.ድ ሰላም አስከባሪ

    ወታደሮች ተጠያቂነት ዙሪያ አጀንዳ ለውይይት

    ያቀረበችውም በዚሁ በፕሬዚዳንትነቷ ወቅት ነበር።

    እ.ኤ.አ በሴፕቴምበር 2017 የፀጥታው ም/ቤት

    ፕሬዚዳንት የነበረችው አገራችን በዚሁ ወር በተካሄደው

    72ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መደበኛ

    ስብሰባ ላይ የወቅቱ የፀጥታው ም/ቤት ፕሬዚዳንት

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠ/ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም

    ደሳለኝ በዓለም መሪዎች የውይይት መድረክ ላይ

    በመገኘት ያነሱት መሰረታዊ ጉዳይ ይሆናል። ይኸውም

    ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ለአፍሪካ ችግሮች መቀረፍ

    መጫወት የሚጠበቅበትን ገንቢ ሚና በመጫወት ረገድ

    ከተራ ቃል መግባት የዘለለ ተግባራዊ ምላሽ ሊሰጥ

    እንዳልቻለ፣ ሆኖም ተግባራዊ ምላሽ መስጠት

    እንደሚኖርበት የሚያስገነዝብ ገንቢ ኃሳብ ማቅረባቸው

    አገራችን በተ.መ.ድ የፀጥታው ምክር ቤት

  • 2

    ተጠቃሽ ነው። አገራችን በዚሁ 72ኛው የመንግስታቱ

    ድርጅት መደበኛ ስብሰባ ላይ ያቀረበችው የፀረ-

    ሽብርተኝነት አህጉር አቀፍ የትግል ስትራቴጂካዊ ሰነድ

    በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አድናቆትን

    ሊያተርፍላት ችሏል። ይህም ሊሆን የቻለው በዓለም

    አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ በመሰማራትና

    ውጤታማ ተግባር በማከናወን ረገድ መልካም ስም ያላት

    አገራችን ሽብርተንነትን ከመታገል አንፃርም ለሌላው

    ዓለም የሚተርፍ ጠቃሚ ልምድ በማዳበሯ ነው።

    አገራችን የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለዓለም

    አቀፍ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ተጋላጭ ተደርገው

    ከሚወሰዱ አካባቢዎች አንዱ ቢሆንም ከሁሉም

    የጎረቤት አገራት ጋር በተሻለ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት

    ውስጥ የምትኖር በመሆኗ ነው።

    አገራችን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር

    ተልዕኮዎችን በተገቢው ስትወጣ ከመቆየቷም ባሻገር

    እ.ኤ.አ በሴፕቴምበር 2017 የፀጥታው ም/ቤት

    ፕሬዚዳንትነቷን ተጠቅማ ያቀረበችው የሰላም ማስከበር

    አጀንዳም 2378/2017 የውሳኔ ሀሳብ ሆኖ

    ተመዝግቧል። የውሳኔ ሀሳቡ የሰላም ማስከበር

    ተልዕኮዎችን በተጠያቂነት፣ በግልጽነትና ውጤታማነት

    በላቀ ሁኔታ እንዲፈጸም ለማድረግ ያለመ ነው።

    አገራችን ያቀረበችው ሰላም ማስከበር አጀንዳ

    ያካተታቸው የማሻሻያ ሀሳቦች የተመድ የሰላም ማስከበር

    ተልዕኮ ከሌሎች ተግባሮች መነጠል እንደሌለበትና አባል

    አገራት ግጭት ከመከሰቱ በፊት በመከላከል ላይ ማተኮር

    እንደሚገባቸው፣ የሰላም ማስከበር ተግባር በተ.መ.ድ

    ብቻ ሊከናወን የማይቻል በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራር

    መዘርጋት እንዲሁም የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ የሚሉት

    ይገኙበታል። በተለይም ሰላምና መረጋጋት በተለያቸውና

    የተ.መድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በተሰማሩባቸው

    የአፍሪካ አገራት ከማንኛውም የኃይል ጥቃት

    ሊታደጓቸው የሚገባቸው ሴቶች ላይ የሚፈጸመው

    አስነዋሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ በቸልታ መታለፍ

    እንደሌለበት አገራችን አሳስባለች።

    አገራችን የፀጥታው ም/ቤት ፕሬዚዳንትነት ቆይታዋ

    በማሊ፣ ሊቢያ፣ ኮሎምቢያ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ በዓለም አቀፍ

    ሰላም ማስከበር ተልዕኮ እና ፀረ-ሽብርተኝነት (በተለይም

    IS በተሰኘው ሽብርተኛ ቡድን ተጠያቂነት) ላይ

    ውሳኔዎች ተላልፈዋል። በተለይ የተ.መ.ድ የፀጥታው

    ም/ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ የጣለበት

    ስብሰባ የተካሄደው እ.ኤ.አ በሴፕቴምበር 2017

    በአገራችን የም/ቤቱ ፕሬዚዳንትነት ወቅት ነው። ሰሜን

    ኮሪያን በተመለከተ በተጠራው በዚሁ ጉባኤ አገራችን

    የፀጥታው ም/ቤት ሰሜን ኮሪያን ወደ ሰላም ድርድር

    ለማምጣት ማንኛውንም አማራጭ እንዲጠቀም

    ጠይቃለች። ይህ ክስተት አገራችን በሰሜን ኮሪያ ልሳነ

    ምድር ግማሽ ምዕተ ዓመት ያለፈው ቀውስ ጋር

    የሚያቆራኝ የታሪክ ግጥምጥሞሽ ያስታውሰናል። ይህም

    የሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት

    ቀደምት የተባበሩት መንግስታት አባል አገራት ደቡብ

    ኮሪያን ደግፈው ሲሰለፉ ሀገራችንም የራሷን ሰላም

    አስከባሪ ወታደሮች አዝምታ እንደነበር በታሪክ

    አይዘነጋም። የሰሜን ኮሪያ የኒውክለር ጦር መሳሪያ

    ተደጋጋሚ ሙከራዎች ዓለማችንን ስጋት ላይ በጣለበት

    በዚህ ወቅት የተ.መ.ድ ፀጥታው ም/ቤት ሰሜን ኮሪያ

    ላይ ማእቀብ ለመጣል የተገደደበትን መድረክ አገራችን

    በፕሬዚዳንትነት ልትመራ መቻሏ ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ

    ያሰኛል።

    የፀጥታው ም/ቤት ሰሜን ኮሪያን ወደ ሰላም ድርድር

    ለማምጣት ማንኛውንም አማራጭ እንዲጠቀም

    አገራችን በዚህ ዓለምአቀፍ መድረክ በዚህ ደረጃ

    እንድታነሳ ያደረጋት ሚስጢር ለዓለም ሰላምና ደህንነት

  • 3

    መረጋገጥ ላበረከተችው አስተዋፅኦ በዓለም አቀፉ

    ማህበረሰብ የተሰጠ የዕውቅና መገለጫ መሆኑ

    አያጠያይቅም። የዚህ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ደግሞ

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲና

    ስትራቴጂ ውጤት ነው። ይህ ከጎረቤት አገራት ጀምሮ

    ከመላው አፍሪካ (ከኤርትራ መንግስት በስተቀር) እና

    ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በተፈጠረው መልካም

    ግንኙነትና ለዓለም ሰላም ባበረከትነው አስተዋጽኦ

    እንዲሁም በገነባነው መልካም ገፅታ የተረጋገጠ ነው።

    በተጨማሪም አገራችን ትኩረት እንዲያገኙ የተመረጡ

    ሁለት ፕሮግራሞችን በተለይ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና

    ፀጥታ ም/ቤት ጋር በአዲስ አበባ የተካሄደው የጋራ

    ስብሰባ፣ እንዲሁም የተ.መ.ድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮን

    ለማጠናከር የተካሄደው ስብሰባ አስራ አምስቱ

    የፀጥታው ም/ቤት አባላት በተገኙበት ተዘጋጅቷል።

    ከመቶ ዓመታት በፊት በቅኝ ገዢዎች ላይ በተጎናፀፈችው

    አንጸባራቂ የአድዋ ድል ለመላው አፍሪካውያን የኩራት

    ምንጭ የሆነችው አገራችን ባለፉት ሁለት አስርት

    ዓመታት ደግሞ ስኬታማ የኢኮኖሚ ሞዴል ተደርጋ

    መታየት ጀምራለች። አገራችን አፍሪካውያን ወገኖቻችን

    ግጭት ውስጥ ሲገቡ ግንባር ቀደም ደራሽ ለመሆን

    ችላለች። ከሩዋንዳ እስከ ቡሩንዲ፣ ከሶማሊያ እስከ

    ላይቤሪያ፣ ከደቡብ ሱዳን እስከ ሱዳን ባሉ ግጭቶች

    ከየትኛውም አገር በፊት ደርሳ የሰላም ማስከበር

    ዓለምአቀፍ ኃላፊነቷን በመወጣት ሰላምና መረጋጋት

    በማስፈን ቁልፍ ሚና ተጫውታለች፣ በመጫወትም ላይ

    ትገኛለች።

    በጋራ ተጠቃሚነት መርህ በኢነርጂ ልማትና በድንበር

    ተሻጋሪ ወንዞቿ አጠቃቀም ላይ በተከተለችው አርቆ

    አስተዋይነት በጥርጣሬ ይመለከቷት ከነበሩ መንግስታት

    ሳይቀር የተሻለ ግንኙነት ልትፈጥር ችላለች። ይህ ጥረት

    አገራችን ከነባርም ሆነ ከአዳዲስ ጎራዎች ነፃነቷን

    አስጠብቃ የማንም ተቀጥላ ሳትሆን በመንቀሳቀሷና

    ለጋራ ጥቅሞች በመሰለፍ ረገድ አስተማማኝ አጋር

    መሆኗን በማረጋገጧ ከሁሉም ልእለ ሃያላን ሳይቀር በጎ

    ግንኙነት ለመመስረት አስችሏታል።

    አገራችን የተ.መ.ድ የፀጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባል

    መሆኗ በተለይም እ.ኤ.አ በሴፕቴምበር 2017

    የም/ቤቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ኃላፊነቷን በአግባቡ

    መወጣቷ የአገሪቱን ተደማጭነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት

    እንዳሳደገ ዕሙን ነው። ይህም የአገሪቷን የሁለትዮሽም

    ሆነ የባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን

    በማስፋት ከፀጥታው ም/ቤት አባላት ልምድ ለመውሰድ

    ከማስቻሉም በላይ ያለፈው አንድ አመት የም/ቤቱ

    ቆይታዋን በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እንደ ትልቅ ስኬት

    መውሰድ ይቻላል። በአጠቃላይ ሲታይ አገራችን በዓለም

    አቀፍ ግንኙነቷ ከሁሉም ጋር ፍቅርና ትብብርን

    የምታስቀድም አገር መሆኗ በሁለትዮሽም ሆነ በባለ ብዙ

    ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶቿ አማካኝነት

    ተጠቃሚነታችንን ማስፋት ተችሏል።

    ለዚህ ስኬት መሰረቱ ዲፕሎማሲያችን ድህነትና

    ኋላቀርነታችን ዋነኛ ጠላቶቻችን እንደሆኑ በመቀበል

    በህዝብ ጥረት ለማስወገድ በተቀረፀ ፖሊሲ የሚመራ

    በመሆኑ ነው። የውጭ ግንኙነታችን የተመሰረተው

    ድህነትና ኋላቀርነትን በማጥፋት ትግል ላይ መሆኑ

    ዕሙን ነው። ይህ በጠንካራ ብሄራዊ ጥቅም ላይ

    የተመሰረተው የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ አገራችንን

    ከመቸውም ጊዜ የላቀ ተቀባይነት እንዲኖራትና አገራዊ

    ጥቅሟን እንድታሰፋ አስችሏታል። ይህም ከዓለምአቀፉ

    ማህበረሰብ ጋር በፈጠርነው መልካም ግንኙነት እና

    በአለምአቀፍ ሰላም ማስከበር ረገድ ባበረከትነው

    አስተዋጽኦ እንዲሁም በገባነው መልካም ገጽታ

    ተረጋግጧል። በዚህ ረገድ አገራችን ያገኘችውን ስኬት

    በቀሪው አንድ ዓመት የፀጥታው ምክር ቤት ቆይታዋም

    ሆነ በሌሎች የባለብዙ ወገን ግንኙነቶቿ አጠናክራ

    የምትቀጥል ይሆናል።

    ስለሆነም አገራችን በዓለም አቀፍ መድረክ

    የምታካሂዳቸውን የሁለትዮሽም ሆነ የባለ ብዙ ወገን

    ግንኙነቶቿን የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ

  • 4

    ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሀገር

    ውስጥ በሚካሄዱ ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች

    ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የአገራችንን ህዳሴ ዕውን

    እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በህዝብ

    ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ አመት የስራ

    ዘመን አንደኛ የጋራ መደበኛ ስብሰባ ላይ የመክፈቻ

    ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ የ2016/17

    የሴክተሮች ዕቅድ አፈጻጸምን በመዳሰስ የ2010 በጀት

    አመት ዋነኛ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ

    ስራዎችን እና የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫዎች

    ለምክር ቤቶቹ አባላት ገልጸዋል᎓᎓

    ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ አገራችን በምትከተለው

    የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተሀድሶ መስመር ፍትሀዊና

    ዘላቂነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ ከጀመረች አስራ

    አምስት አመታት እንደተቆጠሩና በአዲሱ የኢትዮጵያ

    ሚሊኒየም የመጀመሪያዎቹ አስር አመታት በአማካይ

    የ10.5 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ በአለም ፈጣን

    ዕድገት ካስመዘገቡ ሀገሮች ተርታ መሰለፍ መቻሏን

    ጠቅሰው የአዲሱን ሚሊኒየም ሁለተኛውን አስር አመት

    በተመሳሳይ የዕድገት ፍጥነት በማሰቀጠል መካከለኛ ገቢ

    ያላት ሀገር እንደምትኖረን እርግጠኛ ነን ብለዋል᎓᎓

    ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው በሁለተኛው የዕድገትና

    ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሁለተኛ አመት ያጋጠሙ

    ተግዳሮቶችንና የተገኙ ውጤቶችን በዝርዝር ገልጸዋል᎓᎓

    በ2009 ዓ.ም ኢኮኖሚያችን በአመቱ በአማካይ

    የ10.9% ዕድገት ማስመዝገቡን፣ ለዚሁ ዕድገት ግብርና

    36.3%፣ ኢንዱስትሪ 25.6% ከዚህም ውስጥ

    ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የ6.4% እና የአገልግሎት

    ዘርፍ የ39.3% ድርሻ እንዳላቸው ይህም ኢኮኖሚያችን

    መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ መጀመሩን አመላካች

    መሆኑን ተናግረዋል᎓᎓

    በ2016/17 በአንድ በኩል በኢኮኖሚያችን የተካሄደው

    የኢንቨስትመንት አፈጻጸም የሀገር ውስጥ ምርትና

    ምርታማነት ዕድገት፣ የስራ ስምሪትና የድህነት ቅነሳ ጋር

    ተያይዘው ለተቀመጡት ግቦች መሳካት አዎንታዊ

    አስተዋጽኦ እንደነበረው፣ በሌላ በኩል በግብርናው ላይ

    አሉታዊ ተጽእኖ የፈጠረውን በተከታታይ የተከሰተውን

    ድርቅ ለመቋቋም የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብትና ውሀን

    ማዕከል ያደረገ የመስኖ ግብርናን ይበልጥ ለማስፋፋት

    ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ እንዲሁም የአነስተኛና

    ጥቃቅን ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ወደ መካከለኛና

    ትላልቅ ኢንዱስትሪ በፍጥነት እንዲያድግ ርብርብ

    ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል᎓᎓

    በ2017/18 መጨረሻ ላይ የማኑፋክቸሪንግ

    ኢንዱስትሪ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ያለውን

    ድርሻ ወደ 7% ማሳደግ፣ የአምራች ዘርፎች ከፍተኛ

    ዋጋ የሚያወጡ ምርቶች ላይ በማተኮር የእሴት

    ጭማሪውን ይበልጥ እንዲያጎለብቱ መስራት እንዲሁም

    የአነስተኛ ማሳ ግብርና ልማትን ማዘመንና የተማሩ

    ወጣቶችና የግሉ ባለሀብት በግብርና ስራ ላይ ይበልጥ

    እንዲሰማሩ የሚሰራ ማድረግ የአመቱ ዋነኛ የትኩረት

    አቅጣጫ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል᎓᎓ በዚህም

    መሰረት በ2017/18 የ11.1% አመታዊ አማካይ

    ዕድገት በማስመዝገብ ፈጣንና ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ዕድገት

    ለማስቀጠል ታቅዷል᎓᎓ ግብርና በርካታ የህብረተሰብ

    ክፍል የሚሳተፍበትና የዕድገታችን ምንጭ በመሆኑ

    የ2017/18 ህዳሴ ጉዞ ፍኖተ ካርታ

  • 5

    ቢያንስ የ8.0% ዕድገት እንዲያስመዘግብ ይጠበቃል᎓᎓

    የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ለማቀላጠፍ

    ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልዩ ትኩረት

    በመስጠት የጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ

    ኢንዱስትሪዎች 22.6%፣ የትላልቅ ኢንዱስትሪዎች

    21.8% እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ 23%

    እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉ 11% ዕድገት

    እንዲያስመዘግብ ታቅዷል᎓᎓

    በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የዋጋ

    ንረት በነጠላ አሀዝ እንዲገደብ አቅጣጫ መቀመጡ

    ይታወቃል᎓᎓ በዚህም መሰረት የተረጋጋ የማክሮ

    ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲኖር ተግባራዊ የተደረጉ የፊስካልና

    የገንዘብ ፖሊሲዎች እንዲሁም የተወሰዱ እርምጃዎች

    የተፈለገውን ውጤት ማስገኘታቸው፣ የአገር ውስጥ

    የፋይናንስ አቅምን በማጠናከር ከታክስና ሌሎች

    ምንጮች የሚገኙ ገቢዎች በአግባቡ መሰብሰቡ፣

    የመንግስት ወጪዎች ፍትሀዊ የሀብት ድልድልን

    በሚያረጋግጥ መልኩ መፈፀሙ እና የታክስና የጉምሩክ

    ፖሊሲዎች ገቢ ከማስገኘት ባለፈ የኢንዱስትሪ

    ልማትንና ኤክስፖርትን እንዲያበረታታ ጥረት መደረጉ

    ተመልክቷል᎓᎓ በተመሳሳይ የመንግስት የበጀት ጉድለት

    ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ድርሻ ወደ 3% አካባቢ

    እንዲሆን ታቅዶ የተሻለ አፈጻጸም (2.5%)

    ከመመዝገቡ ባሻገር አሸፋፈኑም የሀገር ውስጥ

    ምንጮችን አሟጦ በመጠቀም መሆኑ በአዎንታዊ

    መልኩ ተገልጿል᎓᎓

    ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የ2016/17 ዓ.ም

    የገንዘብ ፖሊሲና የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ልማት ትኩረት

    ያደረገው ሚዛናዊ የገንዘብ አቅርቦትና ዝውውር

    በማረጋገጥ የተረጋጋና በነጠላ አሀዝ የተገደበ የዋጋ

    ግሽበት እንዲኖር በማድረግ የወጭ ንግድን

    ለማበረታታትና መዋቅራዊ ሽግግርን ለማፋጠን

    እንዲቻል መሆኑን ጠቅሰዋል᎓᎓ በ2017/18 ዓ.ም

    በአዲስ መልክ የተጀመረው የታክስ ሪፎርም ስራ

    በተለይም በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ላይ በማተኮር

    መስራት፣ ለኤክስፖርት ገቢያችን 80% አስተዋጽኦ

    የሚያበረክቱትን ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ

    ቅመም፣ አበባና የቁም እንስሳት በመጠንና በጥራት

    ማሳደግ፣ በማዕድን ዘርፍ ወርቅና ሌሎች ጌጣጌጥ

    ማዕድናት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማዕከል

    በማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ኤክስፖርት

    በፍጥነት ማሳደግ በበጀት አመቱ ትኩረት

    እንደሚሰጠውና ይህንንም ለማበረታታት በጥናት ላይ

    የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ እንደሚደረግ

    ገልጸዋል᎓᎓

    የሀገራችን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ

    ትራንስፎርሜሽንን የሚያግዝበት አንዱ መንገድ ቁጠባን

    በማበረታታት ሲሆን ባሳለፍነው አመት ባንኮች በርካታ

    ቅርንጫፎቻቸውን በመክፈት ለህዝቡ ተደራሽ መሆን

    በመቻላቸው የባንኮች ተቀማጭ በ23% ማደግ

    መቻሉና በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን

    መጨረሻ ቁጠባ ከሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት ያለው

    ድርሻ ወደ 29% እንዲያድግ ለማድረግ የፖሊሲ

    ድጋፎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑ ተመልክቷል᎓᎓

    ስትራቴጂያዊ የምግብ ሰብሎችን በጥራት፣

    በምርታማነትና በተወዳዳሪነት ለማሳደግ መንግስት

    በትኩረት እንደሚሰራ የተገለጸ ሲሆን በ2017/18

    ለአርሶ አደሩና ከፊል አርሶ አደሩ የሚሰጠው

    የኤክስቴንሽን አገልግሎት ከተሟላ የምርጥ ዘር

    አቅርቦትና የቴክኖሎጂ ምክረ-ሀሳብ ጋር እንዲሆን

    ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ እንዲሁም የሀገር በቀል

    ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ትኩረት

    በመስጠት የግብርና ሜካናይዜሽን ተጠናክሮ

    እንደሚሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል᎓᎓

    ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚያችንን መዋቅራዊ

    ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው᎓᎓ የሰው

    ጉልበትን በስፋት የሚጠቀሙና ኤክስፖርት መር የሆኑ

    ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ላይ ትኩረት

    ተሰጥቷል᎓᎓ በዚህም ትላልቅ የውጭ እና ሀገር በቀል

    ኩባንያዎች በዘርፉ በስፋት እንዲሰማሩ ድጋፍ

  • 6

    እንደሚደረግ፣ ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው የጨርቃ

    ጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የምግብና

    መጠጥ እና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች

    ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና የነባር ፋብሪካዎች አቅም

    እንዲሻሻል በማድረግ በአለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ

    ምርቶች እንዲመረቱ ለማስቻል እየተሰጠ ያለው ድጋፍ

    ተጠናከሮ እንደሚቀጥል እንዲሁም የኢንዱስትሪ

    ፓርኮች ልማት ስራ በበጀት አመቱ በጥራት

    እንደሚስፋፋ ተመልክቷል᎓᎓

    የኢኮኖሚያችንን ተወዳዳሪነት ከሚወስኑት ጉዳዮች

    አንዱ የሆነውን የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ጥራት

    ማሳደግ ሌላው በበጀት አመቱ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ

    ነው᎓᎓ መንግስት የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን

    ለመሙላት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል᎓᎓

    በ2016/17 የገጠር መንገድ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ

    በተሰራው ስራ ወደ 75% የሚሆኑ የገጠር ቀበሌዎች

    እርስ በእርስ እና ከዋና ዋና መንገዶች እንዲገናኙ የተደረገ

    ሲሆን፣ በ2017/18 ስራውን ወደ 85% ለማድረስ

    እንደሚሰራ እንዲሁም በግንባታ ላይ ያሉ የባቡር

    መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚከናወኑ

    ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል᎓᎓

    ሌላው ወሳኝ መሰረተ ልማት የሆነው የኤሌክትሪክ

    ሀይል አቅርቦት በተመለከተም የጊቤ -3 ሀይል ማመንጫ

    በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ ማድረግ፣ ስልሳ በመቶ

    የደረሰውን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ

    ማፋጠን እንዲሁም በሂደት ላይ የሚገኙ የተለያዩ

    የታዳሽ ሀይል ፕሮጀክቶች ስራ ማፋጠን ትኩረት

    የሚሰጠው ሲሆን መንግስት ከሚያከናውነው የሀይል

    ማመንጨት ስራ በተጨማሪ በቀጣይ የህዝብ ተወካዮች

    ም/ቤት ያፀድቀዋል ተብሎ በሚጠበቀው የመንግስትና

    የግሉ ዘርፍ አጋርነት (Public Private

    Partnership - PPP) ህግ መሰረት የግሉ ዘርፍ

    በሀይል ማመንጨቱ ስራ እንዲሳተፍ ይደረጋል᎓᎓

    የዲጂታል መሰረተ ልማት አቅርቦት በኢንፎርሜሽን

    ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የተጀመረው

    ስራ ተጠናክሮ በገጠር የኢንተርኔትና የመረጃ ፍላጎትን

    ለማሟላት የሚያስችሉ ማዕከላትን በማደራጀት ሽፋኑን

    ከ12% ወደ 40% ለማድረስ እንደሚሰራ

    ተመልክቷል᎓᎓

    ሌላው ትኩረት የተሰጠው የማህበራዊ ዘርፍ ስራዎች

    ሲሆን በትምህርት ረገድ በሁሉም እርከኖች የትምህርት

    ተሳትፎ በማሳደግ ከፍተኛ ውጤት ቢመዘገብም የጥራት

    ችግር አሳሳቢ በመሆኑ በበጀት አመቱ ተጠናክሮ

    እንደሚሰራ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና

    በእያንዳንዱ ወረዳ እንዲስፋፋ እንዲሁም

    የዩኒቨርስቲዎች ግብአት የማሟላት ስራ እንደሚሰራ

    በንግግራቸው ተመልክቷል᎓᎓ በተያያዘም በጤናው

    ሴክተር መሰረታዊ ጤና አገልግሎት ለመስጠት

    የተሰራው ስራ ውጤታማ እንደሆነ ተጠቅሶ

    በ2017/18 ዓ.ም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን

    መከላከል፣ ጥራቱ የተጠበቀ የሆስፒታል አገልግሎት

    ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም የመድሀኒት አቅርቦት

    ማሻሻል ትኩረት የተሰጣቸው ስራዎች ናቸው᎓᎓

    አዲሱ አመት የመንግስትን የማስፈጸም አቅም

    በመገንባትና የህዝቡን ተሳትፎና ባለቤትነት በማጎልበት

    መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት

    የሚደረግበት አመት እንደሚሆን አቅጣጫ ተቀምጧል᎓᎓

    ይህን አስመልክቶ ፕሬዚዳንቱ የተሀድሶ እንቅስቃሴው

    ይበልጥ ጥልቀት እንዲኖረውና የስርአቱ አደጋ የሆነውን

    ያለ ውድድር እና ያለአግባብ የመጠቀም እንዲሁም

    የሙስና ዝንባሌና ተግባር ለመቆጣጠር በጥልቀት

    የመታደስ ንቅናቄ ታውጆ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ

    መደረጉን ጠቅሰው፣ ህዝቡ በስፋት እንዲወያይና የትግሉ

    ባለቤት እንዲሆን በተሰራው ስራ የታዩት መልካም

  • 7

    ውጤቶች እንዲሰፉ ማድረግ የበጀት አመቱ ዋናው ስራ

    እንደሆነ ገልጸዋል᎓᎓ ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም መላው

    የፖለቲካ አመራሮች እና የመንግስት ሰራተኞች

    ሀላፊነትና ስራቸውን በቅንነት፣ በትጋትና በታማኝነት

    እንዲያገለግሉ አቅማቸውን ለማጎልበት የሚሰራ

    መሆኑን፣ ሙስና ጎልቶ በሚታይባቸው አገልግሎቶች

    ዙሪያ የተጀመሩ የሪፎርም ስርአቶች በ2017/18 ወደ

    የተሟላ ትግበራ እንደሚገባ እንዲሁም በሙስና ተግባር

    ላይ የተሰማሩ ሁሉ በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ

    የተጀመረው ስራም በጥናት ላይ ተመስርቶ ተጠናክሮ

    እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል᎓᎓

    የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ለማሳደግና የፌዴራላዊ

    ዴሞክራሲያዊ ስርአቱን ለመገንባት የሚያስችሉ

    አዋጆችና ፖሊሲዎች በበጀት አመቱ እንደሚፀድቁ፣

    በምርጫ ስርአቱ ላይ ሊደረግ የታሰበው ማሻሻያ

    በዘንድሮ አመት ለም/ቤት እንደሚቀርብና በ2019/20

    ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ እንዲደርስ የሚደረግ

    መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል᎓᎓ በ2017/18

    በመላው አገሪቱ የሚካሄደው የአካባቢ እና ማሟያ

    ምርጫ ዴሞክራሲያዊነቱን ጠብቆ ነፃ፣ ፍትሀዊና በህዝቡ

    ዘንድ ተአማኒነትን ያተረፈ እንዲሆን መንግስት

    አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑ ተመልክቷል᎓᎓

    በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንዲጎለብት

    የፖለቲካ ምህዳሩም ይበልጥ እንዲሰፋ ገዥው ፓርቲ

    ኢህአዴግ እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጀመሩት

    ውይይትና ድርድር በተስማሙበት መርህና መርሀግብር

    መሰረት እየተጓዘ እንደሚገኝና መንግስት ሁሉም

    ያገባኛል የሚሉ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ

    ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ሁሌም በሩን ክፍት አድርጎ

    ለሂደቱ ስኬታማነት የሚሰራ መሆኑን ፕሬዚዳንት ዶ/ር

    ሙላቱ ተሾመ በድጋሚ አረጋግጠዋል᎓᎓ የሚዲያ

    ተቋማትም በሀገራችን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ

    የበኩላቸውን በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የተጀመረው

    የሚዲያ ሪፎርም ስራ በበጀት አመቱ ተጠናክሮ

    እንደሚሰራ ተገልጿል᎓᎓

    በ2009 ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ

    የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ እንደነበርና ከህዝቡ ጋር

    በተደረገ ሰፊ ውይይት በተፈጠረው መግባባት የሀገራችን

    ሰላም ወደ ነበረበት በመመለሱ አዋጁ እንዲነሳ መደረጉን

    ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ሰላማችንን አሁንም አጠናክረን

    ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል᎓᎓ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ

    ሶማሌ አካባቢ አፍራሽ አመለካከቶች በወለዷቸው

    ግጭቶች የሰው ህይወት ያለፈበትና ንብረት

    የወደመበትን አሳዛኝ ክስተት ያነሱት ፕሬዚዳንቱ

    መንግስት ፀጥታውን ከማስከበር ባሻገር አጥፊዎችን ወደ

    ህግ ለማቅረብ ሳይታክት እየሰራ እንደሚገኝ

    ተናግረዋል᎓᎓ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መልሶ

    እንዲቋቋሙ ለማድረግ ህዝቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆም

    ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በ2017/18 እንደዚህ አይነት

    በህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አንድነት

    የሚያፈርስ ተግባር በጭራሽ ሊፈቀድ የማይገባው

    መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል᎓᎓

    ወጣቶችና ሴቶች በሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ውስጥ

    የማይተካ ሚና ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው᎓᎓

    ባለፈው አመት የወጣቶችን እኩል ተሳታፊነትና ፍትሀዊ

    ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዋና ስራ ተደርጎ በተካሄደው

    እንቅስቃሴ የወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ስትራቴጂ

    ማስፈጸሚያ ፓኬጅ ተከልሶ እንዲዘጋጅ ተደርጓል᎓᎓

    ይህንን የለውጥና ዕድገት ፓኬጅ ወደ ስራ ለማስገባት

    የፌዴራል መንግስት ከመደበው 10 ቢሊዮን ብር

    የወጣቶች ፈንድ በተጨማሪ ክልሎችም በተመሳሳይ

    መልኩ በድምሩ ወደ 10 ቢሊዮን ብር መድበው

    በተደረገ እንቅስቃሴ እስካሁን ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ

    ወጣቶች ስራ መፍጠር መቻሉን ገልፀዋል። በበጀት

    አመቱ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር ተጠናክሮ እንዲሰራ

    አንዱ የመንግስት ትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ

    ተመልክቷል᎓᎓ በተያያዘም ሴቶች በሀገራችን በሚካሄዱ

    ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች

    የሚያደርጉትን ተሳትፎ በማጠናከር በተለይ የገጠር

    ሴቶች ከመሬት ባለቤትነት የጋራ መብት መጎናፀፍ ባሻገር

    በተጓዳኝ በግብርና ስራዎች የተገኘውን ለውጥ በማስፋት

  • 8

    እና የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት

    ተሳትፎአቸውን በማሳደግ የሴቶችን ሁለንተናዊ

    ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ

    ተመልክቷል᎓᎓

    የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመተግበር ቀዳሚ

    በመሆን ተጠቃሽ የሆነችው ሀገራችን በአለም አቀፍ

    መድረክ ያላት ተሰሚነት በመጨመሩ በአሁኑ ወቅት

    ሁለት ታላላቅ የአለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ

    መድረኮችን በሊቀመንበርነት እየመራች እንደምትገኝ

    መረጃዎች ያመለክታሉ᎓᎓ ከዚሁ ጋር በተያያዘም

    ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ሀገራችን የቀረፀችው

    ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት

    ስትራቴጂ በየክፍላተ-ኢኮኖሚው ዕቅድ ውስጥ ተካቶ

    እንዲተገበር እየተደረገ እንደሚገኝና ውጤትም

    እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በበጀት አመቱ

    ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል᎓᎓ በመጨረሻም

    የኢፌዲሪ መንግስት የሀገራችንን ሰላምና ልማት ይበልጥ

    በማረጋገጥ በመንግስትና በህዝብ የተቀናጀ ርብርብ

    የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመረውን

    የህዳሴ ጉዞ ዳር ለማድረስ ቁርጠኛ መሆኑን ለምክር

    ቤቶቹ አባላትና ለመላው የአገራችን ህዝቦች

    አረጋግጠዋል᎓᎓

    የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ኦክቶበር 9

    ቀን 2017 ለህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር

    ቤቶች የስራ ዘመን መክፈቻ ላይ ያቀረቡት የበጀት አመቱ

    ዕቅድና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ላይ ምክር ቤቶቹ

    ኦክቶበር 26 ቀን 2017 ተወያይተዋል᎓᎓ ከምክር

    ቤቶቹ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር

    ሀይለማርያም ደሳለኝ ምላሽ እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ

    ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡት

    የመንግስት የ2017/18 ረቂቅ ዕቅድ ፀድቋል᎓᎓

    አገራችን ኢትዮጵያ እንደ ነዳጅና ማዕድን ያሉ የተፈጥሮ

    ሀብቶችን መሰረት ሳያደርጉ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት

    እያስመዘገቡ ካሉ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗ

    ይታወቃል፡፡ ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ

    የበላይነቱን ለረዥም ዓመታት ተቆጣጥራ ከቆየችው

    የጐረቤት አገሯ ኬኒያ የመሪነቱን ስፍራ መረከቧን ዓለም

    አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በ2017 ባወጣው ሪፖርት

    መዘገቡም ይታወሳል።

    አገሪቷ እያስመዘገበች ባለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት

    ምክንያትም በርካታ ዜጎቻችንን ከድህነት ማውጣት

    ተችሏል። ለዚህም እንደ ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃግብር

    ባሉ ድህነት ተኮር ፕሮግራሞች ላይ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ

    ሥራዎች የተገኘ ስኬት እንደሆነ ይታመናል። ይህም

    አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ

    ለመሰለፍ አቅዳ እያደረገች ያለው ሁሉን አቀፍ

    እንቅስቃሴ ማሳያ ነው።

    ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት መንግስት ኢኮኖሚውን

    ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሸጋገር

    የሚያስችል ሰፊ አንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

    በተለይም የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለኢኮኖሚያዊ ሽግግሩ

    የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት

    ለዘርፉ መስፋፋት መሰረት የጣለውን የመጀመሪያውን

    የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ነድፎ ተግባራዊ

    ተደርጓል፡፡ በዚህም በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በጨርቃ

    ጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በምግብና

    መጠጥ ፣ በኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች፣ በወረቀት፣

    በፕላስቲክና በግንባታ መሳሪያዎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች

    ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሉ

    በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን

    የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ከነበረው

    ድርሻ 10 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 14 ነጥብ 3 በመቶ ማሳደግ

    ተችሏል።

    የኢንዱስትሪ ካርክ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው

  • 9

    በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመንም

    ብዙ የሰው ኃይል የሚፈልጉ፣ የውጭ ገበያን መሰረት

    ያደረጉና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት የሚችሉ

    (Import Substitution) ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት

    እቅድ ታቅዶ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም

    የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉን ያሳድጋሉ ተብለው

    ከተለዩት የልማት ሥራዎች ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርክ

    ግንባታ በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የሀገሪቱ ኢንዱስትሪ

    ልማት ስትራቴጂ በግብርና መር ኢንዱስትሪ ፖሊሲ

    (Agricultural Development Led

    Industrialization Policy) ላይ ተመስርቶ

    የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ፣

    ንግድን በማስፋፋት እና የውጭ ምንዛሪ ገቢን

    በማሳደግ፣ ለበርካታ የሰው ኃይል የስራ እድል መፍጠር

    የሚችሉ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች

    በመተካት ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ልማት አስተዋፅኦ

    እንደሚያደርግ ታቅዶ ወደ ተግባራዊ ሥራ ተገብቷል፡፡

    ለዚህም መንግሥት በዕቅድ ዘመኑ 10 የኢንዱስትሪ

    ፓርኮችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመገንባት

    አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። የፓርኮቹ መገንባት

    የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የውጭ

    ንግዱን እንቅስቃሴ ለማነቃቃት አይነተኛ ሚና

    ይኖረዋል፡፡ በቅርቡ ምርታቸውን ወደ ውጭ መላክ

    የጀመሩት የቦሌ ለሚና ቅሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች

    ለሀገራችን የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ጀምረዋል፡፡

    በተመሳሳይ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በቅርቡ

    ለምረቃ የበቁት የኮምቦልቻና መቀሌ የጨርቃጨርቅና

    አልባሳት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው

    በማምረት ኤክስፖርት ማድረግ ሲጀምሩ በአገራችን

    ኢኮኖሚ ግንባታ የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ

    እንደሚሆን እሙን ነው።

    በተጨማሪም በአዳማና በድሬዳዋ ተመሳሳይ

    የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲጠናቀቁ የሃገሪቱን የስራ አጥ

    ቁጥር እንዲቀንስ ከማድረግ ባሻገር ሃገሪቷ ያለባትን

    የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደሚቀርፉ ይጠበቃል።

    የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ለወጣቶች የስራ ዕድል

    በመፍጠር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ

    ይታመናል፡፡ በቅርቡ ወደ ስራ የገባው የሀዋሳ ኢንዱስት

    ፓርክ በአሁኑ ወቅት ለ10 ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ

    ዕድል የፈጠረ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ስራውን ሲጀምር

    ለ60 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ሲጠበቅ፣

    ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን

    የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስገኝ ይታሰባል፡፡ የኢንዱስትሪ

    ፓርኩ አለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው 17 የአሜሪካ፣

    ሲሪላንካ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ህንድና ቻይና ጨርቃ ጨርቅ

    ፋብሪካዎች የያዘ ሲሆን ፓርኩ አገራችን በአፍሪካ

    ቀዳሚ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን

    ላስቀመጠችው ግብ ስኬታማነት ፈር ቀዳጅ ነው፡፡

    በተመሳሳይ የኮምቦልቻ እና የመቀሌ ኢንዱስትሪ

    ፓርኮች ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ ለ50 ሺህ ዜጎች

    የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል፡፡

    የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንደ ቻይና፣ ደቡብ

    ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ማሌዢያና ቬይትናም የመሳሰሉ

    የእስያ ሀገራትን ልምድ መሰረት በማድረግ በመተግበር

    ላይ ሲሆን ዓለማቀፋዊ ደረጃውን ጠብቆ የሀገሪቱን

    የእድገት አቅጣጫ ባማከለ መልኩ ተግባራዊ በመደረግ

    ላይ ይገኛል፡፡ ፓርኮቹ የሚገነቡት በዋና ዋና የአገሪቷ

    የኢኮኖሚ ኮሪደሮች ላይ መሆኑ፣ ከአውሮፕላን

    ማረፊያዎች፣ ከባቡር መስመሮች፣ ደረቅ ወደቦች

    እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቅርብ ርቀት

  • 10

    ላይ እንዲገኙ መደረጉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት

    አገራችን ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት የሚጫወተው ሚና

    ከፍተኛ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

    በተለያዩ የአገራችን ክልሎች በኮርፖሬሽን ደረጃ

    የሚመሩ የግብርና ማቀነባበሪያ የኢንደስትሪ ፓርኮች

    ግንባታ ለማከናወን እቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ በመደረግ

    ላይ ይገኛል። ለማሳያ ያህልም በትግራይ ሁመራ፣

    በኦሮሚያ ቡልቡላ፣ በደቡብ ይርጋለምና በአማራ ቡሬ

    አካባቢዎች የሚገነቡ የተቀናጁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች

    ልማት ይጠቀሳሉ። እነዚህ የግብርና ማቀነባበሪያ

    ኢንደስትሪ ፓርኮች፣ ሀገሪቱ ሰፊ የግብርና እምቅ አቅም

    ያላት ከመሆኑ አንጻር፣ በግብርና ማቀነባበሪያ የሚሰማሩ

    ኢንዱስትሪዎች ጥሬ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት

    በመጨመር በሀገር ውስጥና በውጪ ገበያ እንዲሳተፉ

    ማድረግ ያስችላሉ። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር

    ኢኮኖሚ በሚደረገው ሽግግር የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች

    ሚና ተተኪ የለውም። በዚሁ መሠረት የኢንዱስትሪ

    ፓርኮች ውስጥ ከ15 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው የሀገር

    ውስጥ ባለሃብቶች እንዲያዝ ዕድል ተመቻችቷል።

    የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከተሞች እንዲለሙ፣ ስራ አጥነት

    እንዲቀረፍ፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማሳደግ፣ የአገር

    ውስጥ ምርት እንዲጨምር እንዲሁም የቴክኖሎጂና

    ዕውቀት ሽግግር እንዲስፋፋ በማድረግ ከፍተኛ

    ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እንዳሚኖረው ይታመናል፡፡

    ግብርናን ብቻ መሰረት አድርጎ የነበረውን የሀገሪቱ

    ምጣኔ ሃብት እሴት ተጨምሮበት በአለም አቀፉ ገበያ

    ተወዳዳሪ እንዲሆን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት

    ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚኖራቸው እምነት

    ተጥሎበታል። ‘‘መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ከፍታ ነው’’

    ሲባልም ለአባባሉ እውንነት ስር ነቀል ለውጡ

    የሚኖረው ፋይዳ ከግምት ገብቶ እንደሆነ ሳይታለም

    የተፈታ ነው።

    ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ወጥቶባቸው የተገነቡ

    የኢንዱስትሪ ፓርኮች የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ፤

    በመገንባት ላይ ያሉትና ቀጣይ የሚገነቡትም

    በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ

    የማድረጉ ጉዳይ በዋናነት የመንግስት ሃላፊነት ቢሆንም

    የሁሉም የህብረተብ ክፍል ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ

    አያጠያይቅም።

    በስቶክሆልም የሚገኘው ኢትዮጵያ ኤምባሲ

    ከምሥረታው ጀምሮ በተለያዩ የዲፕሎማሲና ዳያስፖራ

    መስኮች በርካታ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ

    የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ሀገሪቷ

    ከኖርዲክ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር

    ሲሰራ ቆይቷል። ይህ ፅሁፍም ሚሲዮኑ ባለፉት አራት

    ዓመታት ባከናወናቸው አበይት ተግባራት ላይ

    ያተኩራል።

    ባለፉት አራት ዓመታት የኤምባሲውን ጽ/ቤት አመቺ

    ወደ ሆነ የስቶክሆልም አካባቢ በማዛወር የተቀላጠፈ

    አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል መልኩ ተደራጅቶና

    በአንጻራዊነት በቂ የሰው ኃይል ተሟልቶ የተሻለ

    አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በሌላ በኩል ተቀዛቅዞ

    የነበረው የኢትዮ-ስዊድን ግንኙነት ማሻሻል የተቻለ

    ሲሆን፣ ከሌሎች ኖርዲክ አገራት ጋር ያለን ግንኙነትም

    በተመሳሳይ ተጠናክሯል። ለዚህም ከኢትዮጵያም ሆነ

    ከኖርዲክ አገራት በዋናነት ከስዊድን በየጊዜው የሚደረጉ

    የከፍተኛ ባለስልጣናትና የቢዝነስ ማህበረሰቡ የጉብኝት

    ልውውጦች አበይት ማሳያዎች ናቸው። በተመሳሳይ

    በስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድና ኖርዌይ የሚገኙ

    ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ

    የኤምባሲው ያለፉት አራት ዓመታት አፈጻጸም

    ዳሰሳ

  • 11

    ስብስቦች ስር እንዲደራጁ በማድረግ በሀገራቸው ልማት

    እንዲሳተፉና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሚዘጋጁ

    መድረኮች ላይ በማሳተፍ የጋራ መግባባት መፍጠር

    ተችሏል።ከስዊድን ጋር ያለንን የሁለትዮሽ ግንኙነት

    በተመለከተ በተለይ በ2003 ዓ.ም ሚሲዮናችን ወደ

    ቆንስላ ጽ/ቤት የወረደበት ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ

    ቢሆንም ግንኙነቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ በተደረጉ

    ውይይቶች በ2005 ዓ.ም በኤምባሲ ደረጃ ተመልሶ

    እንዲሰራ መደረጉ ይታወሳል። ይህንኑ ተከትሎ

    የሚሲዮኑ መሪ በአምባሳደር ደረጃ መሾሙ ይታወቃል።

    የሚሲዮን መሪውም ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ

    የኤምባሲው ማህበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር

    በመቀናጀት ሀገራችን ከስዊድን ብሎም ከሌሎች ኖርዲክ

    ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ

    ያላሰለሰ ጥረት ተደርጓል።

    በዚህም መሠረት ባለፉት አራት ዓመታት በተሰራው ስራ

    ከስዊድን ጋር ያለን ግንኙነት ታሪካዊነቱን

    የሚያንጸባርቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የሁለቱ ሀገራት

    ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጥንካሬ ከሚያሳዩ ሁኔታዎች

    አንዱ በሀገር ደረጃ የሚደረጉ የጉብኝት ልውውጦች

    ናቸው። ከዚህ አንጻር ባለፉት አራት ዓመታት

    በኢትዮጵያና ስዊድን መካከል በከፍተኛ ባለስልጣናት

    ደረጃ በርካታ የጉብኝት ልውውጦች ተደርገዋል። ዋና

    ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያክል ከስዊድን የሀገሪቱ ጠቅላይ

    ሚኒስትር (በአንድ ዓመት ውስጥ ሶስት ጊዜ)፣ የውጭ

    ጉዳይ ሚኒስትር እና የተለያዩ የሀገሪቱ ፓርላማ አባላት

    እንዲሁም ሌሎች ባለስልጣናት በተለያዩ ጊዜያት

    ሀገራችንን ጎብኝተዋል። ከሀገራችን ወገን የቀድሞ ውጭ

    ጉዳይ ሚኒስትር እና ሚኒስትር ዴኤታ ጨምሮ በተለያዩ

    ሚኒስትሮች የተመሩ የልዑካን ቡድኖች እና ሌሎች

    ባለስልጣናት ባለፉት አራት ዓመታት በስዊድን ኦፊሴላዊ

    ጉብኝት አድርገዋል። በነዚህ ጉብኝቶች ወቅት የጋራ

    ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ

    ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን፣ ውይይቶቹ ካስገኙት

    ውጤቶች መካከል የመግባቢያ ሰነዶች መፈረማቸው፣

    የኢትዮጵያና ስዊድን የአምስት ዓመት የልማት ትብብር

    ስትራቴጂ መፅደቁ እንዲሁም ብዙ የስዊድን ታዋቂ

    ኩባንያዎች በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች

    ለመሰማራት ወደ ሀገራችን መግባታቸው ዋና ዋናዎቹ

    ናቸው።

    አገራችን ከኖርዌይ ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ

    በሁለቱም ሀገራት በኩል በተለያዩ ጊዜያት በከፍተኛ

    ባለስልጣናት ደረጃ የጉብኝት ልውውጦች ተደርገው

    የጋራ መግባባት ለመፍጠር ተሞክሯል። የሁለትዮሽ

    ግንኙነቱን ለማጠናከር ባለፉት አራት ዓመታት ከተደረጉ

    የጉብኝት ልውውጦች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።

    በኖርዌይ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፣ የአካባቢ

    ጥበቃ እና የአየር ንብረት ሚኒስትሩ፣ የኢምግሬሽን

    ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስቴት ሴክሬታሪ

    አገራችንን የጎበኙ ሲሆን፣ በአገራችን በኩል የቀድሞው

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በርካታ ሚኒስትሮ

    ያደረጉትን ጉብኝቶች እንደአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡

    በጉብኝቶቹ ወቅት ባለስልጣናቱ ከአቻዎቻቸውና

    ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የሁለትዮሽና

    አካባቢያዊ ጉዳዮች እንዲሁም በንግድና ኢንቨስትመንት

    ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይቶችን ማካሄድ ችለዋል።

    ኖርዌይ በኢነርጂ ትብብር መስክ ከሀገራችን ጋር

    የትብብር ስምምነት በመፈራረም ሀገራችን በመስኩ

    ለምታደርገው ጥረት በየዓመቱ 60 ሚሊዮን ዶላር

    የልማት ድጋፍ ለማድረግ መወሰኗ፣ ከንግድና

  • 12

    ኢንቨስትመንት አንጻር በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ምርቶች

    ወደ ኖርዌይ ገበያ እንዲገቡ ለማበረታታት ሀገራችን

    የኖርዌይ ፕሪፍሬንሻል ታሪፍ ተጠቃሚ እንድትሆን

    መደረጉ፣ YARA International እና Norfund

    የተባሉ ትላልቅ የኖርዌይ ኩባንያዎች ሀገራችንን የውች

    ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረጋቸው

    ይጠቀሳሉ።

    በሌላ በኩል ከዴንማርክ፣ ፊንላንድና አይስላንድ ጋር

    ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር ባለፉት አራት ዓመታት

    በተሰሩት ስራዎች ሰብዓዊ እርዳታ ላይ ብቻ አተኩሮ

    የነበረው ግንኙነታችን አንድ እርምጃ በመራመድ ወደ

    ኢንቨስትመንት፣ ንግድና የልማት ትብብር እንዲሻገር

    መደረጉ በመስኩ የተከናወነውን ሰፊ ስራ ያሳያል።

    በተለይ ከዴንማርከ ጋር በተያያዘ የዴንማርክ የውጭ

    ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ሀላፊዎች፣ የልማት ትብብር

    ሚኒስትር እና የፓርላማ አባላት አገራችንን

    በመጎብኘታቸው እና በሀገራችንም በኩል ክቡር ጠቅላይ

    ሚኒስትራችን እና የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን

    በዴንማርክ ጉብኝት በማድረጋቸው ዘላቂ የልማት

    ግቦችን (SDGs) መሰረት በማድረግ ለአየር ንብረት

    ለውጥ ስራዎች፣ ለታዳሽ ሀይል ልማት እና ለመሰረተ

    ልማት ኢንቨስትመንት ማስፈጸሚያ 180 ሚሊዮን ዮሮ

    አነስተኛ ወለድ የሚከፈልበት ብድር ስምምነት

    የተፈረመ ሲሆን፣ በንፋስ ሃይል ልማት ዘርፍ 28

    ሚሊዮን የዴኒሽ ክሮነር ማስገኘት ተችሏል᎓᎓

    ፊንላንድም በበኩሏ የኢትዮጵያ የልማት አጋር በመሆን

    ያልተቋረጠ የልማት ፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ላይ

    የምትገኝ ሲሆን፣ ከ2016 እስከ 2019 ለሚካሄዱ የልማት

    ትብብር ፕሮጀክቶች 55 ሚሊዮን ዩሮ በጀት

    መድባለች᎓᎓ ከአይስላንድ ጋር በተለይ በጂኦተርማል

    ዘርፍ ጠንካራ ትብብር በመፍጠር በ2013 የ3.5 ሚሊዮን

    የአሜሪካ ዶላር የልማት ትብብር ስምምነት ከመፈራረም

    በተጨማሪ Rejkjavik Geothermal የተባለ ኩባንያ

    1000MW ኃይል ከጂኦተርማል ለማምረት ከኢትዮጵያ

    ጋር የ4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ስምምነት

    በመፈራረም የፍለጋ ሥራውን እያካሄደ ይገኛል።

    በመሆኑም ከላይ ከተጠቀሱት ውጤቶች በግልጽ

    መረዳት እንደሚቻለው ባለፉት አራት ዓመታት

    ከሁሉም የኖርዲክ ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት ከሰብዓዊ

    እርዳታ ወደ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ትብብር መሻገሩን

    ነው። ይህም ከውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲው

    ብሎም ከኤምባሲው እቅድ አንጻር ሲታይ ትልቅ ስኬት

    ነው። በሌላ በኩል ይህ ስኬት በኤምባሲው ጥረት ብቻ

    ነው የመጣው ለማለት ባያስደፍርም የኤምባሲው ጥረት

    የማይተካ ሚና አለው።

    ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በተጨማሪ ባለፉት

    አራት ዓመታት ኤምባሲው ትልቅ ስኬት ያስመዘገበበት

    ሌላው መስክ የዳያስፖራ ተሳትፎ መስክ ነው።

    ኤምባሲው ለዳያስፖራው የሚሰጣቸው የተለያዩ

    አገልግሎቶች ላይ የነበሩ ክፍተቶች ዳያስፖራው

    ከኤምባሲው ጋር በሚፈለገው ደረጃ ተቀራርቦ

    እንዳይሰራ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። ሆኖም በአሁኑ

    ወቅት በኖርዲክ ሀገራት ውስጥ ባሉ ሁሉም ሀገራት

    በርካታ አዳዲስ የዳያስፖራ አደረጃጀቶችን በመፍጠርና

    ነባሮቹን በማጠናከር ኤምባሲው ወይንም አደረጃጀቶቹ

    ራሳቸው በሚያዘጋጁአቸው መድረኮች ላይ ዳያስፖራው

    በንቃት እየተሳተፈ ለሀገሩ ልማትና ሁለንተናዊ እድገት

    ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። በተለይም

    የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዥ በመፈጸም፣

    በሀገር ቤት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች

    በመሳተፍ፣ የውጭ ምንዛሪ አካውንት በመክፈትና በበጎ

    ስራዎች በመሰማራት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ

    ተችሏል።

    በአጠቃላይ ኤምባሲው ባለፉት አራት ዓመታት

    በሁሉም መስኮች ያሳየው አፈጻጸም ከኤምባሲው እቅድ

    አንጻር ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው። የተገኙ

    ውጤቶች በኤምባሲው ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ ዳያስፖራን

    ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተባብረው በመስራት

    ያስገኙት ውጤቶች ናቸው። ባለፉት አራት ዓመታት

    ሚሲዮኑ በዲፕሎማሲው መስክ ያስመዘገባቸው

    ስኬቶች በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ተግባራት መሰረት

    እንደሚሆኑ ይታሰባል።

  • 13

    ይህን ያውቁ ኖሯል?

    ❖ በዳያስፖራ የመኖሪያ ቤት ልማት ፕሮግራም

    ማዕቀፍ በማሕበር ተደራጅቶ ቤት ለመገንባት

    አመልካቾች ማሟላት ያለባቸው ቅድመ-

    ሁኔታዎች፡-

    1. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት መክፈት፣

    በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ለመክፈት ፡-

    ➢ የባንክ አካውንት ማመልከቻ ፎርም

    መሙላት፣

    ➢ የታደሰ ፓስፖርት ዋናውና ኮፒ፣

    ➢ የመኖሪያ ፍቃድ ዋናውንና ኮፒ፣

    ➢ የውጭ አገር ዜጋ ከሆነ የትውልድ ኢትዮዽያዊ

    መታወቂያ ካርድ እና

    ➢ አንድ ጉርድ ፎቶግራፍ ማቅረብ

    2. በዳያስፖራ የመኖሪያ ቤት ልማት ፕሮግራም

    ለመጠቀም መመዝገብ፡

    ምዝገባውን ለማካሄድ፡-

    ➢ በመመሪያው መሠረት የሚያስፈልገውን

    የገንዘብ መጠን በውጭ ምንዛሪ ገቢ ማድረግ፣

    ➢ ለምዝገባ የተዘጋጀውን ማመልከቻ ቅጽ

    መሙላት እና

    ➢ ሶስት ጉርድ ፎቶግራፍ ማቅረብ

    3. የዳያስፖራ የመኖሪያ ቤት የሕብረት ስራ ማሕበር

    መመሥረት፣

    ማህበሩን ለመመሥረት፡-

    ➢ የማሕበር መመስረቻ ቃለጉባኤ

    ማዘጋጀት፣

    ➢ ማሕበሩን የሚመሩ አመራሮች

    መምረጥ፣

    ➢ የማሕበር መተዳደርያ ደንብ ማዘጋጀትና

    ማሕበሩ ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ

    ማድረግ፣

    4. በማሕበሩ ስም ዝግ አካውንት መክፈትና

    ለግንባታው በአባላት የግል አካውንት ገቢ

    የተደረገውን ገንዘብ ወደ ጋራ ዝግ አካውንት

    ገቢ ማድረግ፣

    5. ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ሲሟሉ

    መረጃዎቹን አጠናቅሮ ወደ ክልል ይላካል፣

    ❖ በተሻሻለው የአማራ ብሔራዊ ክልል የዳያስፖራ

    የመኖሪያ ቤት ልማት ፕሮግራም መመሪያ ቁጥር

    30/2009 መሠረት፡

    ➢ የዳያስፖራ የመኖሪያ ቤት የሕብረት ስራ

    ማሕበራት የግንባታ ቦታ በሚረከቡበት ጊዜ

    የሚከፍሉት የቤት ግንባታ ወጪ 100% መሆኑ

    ቀርቶ 50% እንዲሆንና ቀሪው 50% ደግሞ

    ግንባታው እየተካሄደ እንዲከፈል መወሰኑን፣

    ➢ ማሕበራቱ የግንባታ ቦታ ለመረከብ መቆጠብ

    ካለባቸው 50% ውስጥ ደግሞ በምዝገባ ወቅት

    በሚኖሩበት አገር ባለው የኢትዮጵያ ሚሲዮን

    በኩል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ

    በመክፈት አስቀድሞ 25% ማስቀመጥ እና

    የግንባታ ቦታ በሚረከቡበት ጊዜ ደግሞ

    ቀሪውን 25% መክፈል የሚኖርባቸው መሆኑን

    ያውቁ ኖሯል?

    መንግስት ባመቻቸላችሁ እድል በመጠቀም የቤት ባለቤት ይሁኑ!

    -------------------------- // ----------------------------

    ውድ አንባቢያን በመጽሄቱ ይዘትና ዝግጅት ላይ

    ያላችሁን ጥያቄም ሆነ አስተያየት በኢሜይል

    አድራሻችን [email protected] ወይም

    በስልክ ቁጥራችን +46812048500

    እንድትልኩልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡